ስለሆነው ሁሉ ጎንደር ሁላችሁንም ታመሰግናችኋለች።
ስለሆነው ሁሉ ጎንደር ሁላችሁንም ታመሰግናችኋለች።
ከንቲባ ዘ ጎንደር አቶ ቻላቸው ዳኘው
ወርሃ ጥር ከገባ ጀምሮ ከተማችን ደምቃ፣ ትኩረት ስባና አሸብርቃ ሰንብታለች። ከመላው ዓለምና ከሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎችም እንግዶች ጎንደር እና የጎንደር ሰው ይቀበለናል ብለው መጥተዋል።
ለጥምቀት ቀሚስ ብቻ ሳይሆን ከተማ ቀይረን ሌት ተቀን ደክመን እንግዳዋን በተመቸ ሁኔታ የተቀበለች ከተማ ፈጥረናል። ከሁሉ በላይ ግን በከተማችን ህዘብ ንፁህና ሰው አፍቃሪ ልብ እንኮራለን። በሰላም ወዳድ መንፈሱ እንመካለን።
ተከታታዮቹ አያሌ ኩነቶች ዛሬ በተከበረው የቅዱስ ሚካኤል በዓለ ንግሥና የጥምቀት በዓል ተጠናቋል። በዚህም ከሁሉ በላይ እኔና መላው የከተማው አመራሮች በጎንደር ከተማ ህዝብ ስለኮራን እናመሰግናለን።
በዓሉን ለማክበር ስናስብ በብዙ መልኩ ለደገፋችሁን የክልላችንና የፌዴራል አመራሮች እጅ እነሳለሁ።
ይህ በዓል ከተማ አሰናድተን ልማት አጠናቀን ልናከብር ስንዘጋጅ ሌት ተቀን ጎንደርን በመስራት በተለያየ መልኩ የደከማችሁ ባለሙያዎችም የተሰራ ከተማ ምን እንደሚመስል አሳይታችሁልናል ከልቤ እያመሰገንኩ ያ ፍጥነት፣ ቁጭት እና የስራ ባህል ተጠናክሮ እንዲቀጥል አደራ እላለሁ።
የጎንደር አብያተ ክርስቲያናት ሊቃውንት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ መንፈሳዊ ማኅበራት ጥምረት አባላት እና በጎንደር ጎዳናዎች ምንጣፍ እየተሸከማችሁ ለታቦታቱ ክብር ለደከማችሁ ወጣቶች የጥምቀት በዓል ሁሌም ጎንደር ላይ ደማቅና ታላቅ ነው የሚለውን አስመስክራችኋል። እናከብራችኋለን።
የፀጥታ አካላት ከከተማችን ህዝብ ጋር ተናባችሁ ሌት ከቀን ያለ እረፍት ዘብ ቆማችሁ “በዓሉ በሰላም ስለተጠናቀቀ ደስ ብሎናል” ለማለት አስችላችሁናልና እንኮራባችኋለን።
ይህ ሁሉ ኩነት ያማረው የከተማችን ወጣቶች የሁሉም በዓል ባለቤቶች ስለሆናችሁ ጊዜ ገንዘብ እውቀት ስላፈሰሳችሁ እንደሆነ እንመሰክርላችኋለን።
የሀገራችን ቲክ ቶከሮች ገና ጥር ሲገባ ጀምሮ የጎንደርን መሞሸር አብስራችሁ አነቃቅታችሁናል። ሁላችሁም እንደምታውቁት እናንተ ለጎንደር አደረጋችሁላት እንጂ እኛ ለእናንተ ያደረግነው ነገር የለም። ለዚህ ነው ምስጋናው የሚያስፈልጋችሁ።
በከተማችን የምትገኙ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ከተማችን በጥበብ እንድትደምቅ ስላደረጋችሁ ልትመሰገኑ ይገባል።
የመገናኛ ብዙኃን በእርግጥም የጎንደር ድምቀት የሚዲያ ሽፋን በመስጠት ከዘገባችሁት በተጨማሪ ጎንደርን ናፍቆ ተሳክቶለት ላልመጣ በመላው ዓለምና በሀገር ውስጥ ለሚገኝ ሁሉ በመንፈስ ከእኛ ጋር እንዲሰነብት አድርጋችኋልና እናመሰግናለን። አርቲስቶቻችንና የፊልም ባለሙያዎች እንደ ሙያ ዘርፋችሁ አብራችሁን ስለቆማችሁ ጎንደር ታመሰግናችኋለች።
እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የጎንደር ከተማ ውሃ ልማት፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ የስሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የአማራ ፖሊስ ማርሽ ባንድ፣ የኪን ኢትዮጵያ ቤተሰቦች፣ የከተማችን ሆቴሎች፣ የጎንደር ከተማ ቱሪስት አስጎብኚዎች፣ ሁላችም እንደ ተቋም አበርክቷችሁ ምስጋና ያስፈልገዋልና እጅግ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ።
በተለያዩ ዘርፎች የዝግጅት ኮሚቴው አባላት በመሆን ለደከማችሁ እና ለአሳመራችሁት በሙሉ ድካማችሁ ፍሬ አፍርቷልና እናንተንም እናመሰግናለን። ጎንደር እንዲሁ በዚህ የሰላም እና የድምቀት ድባብ ትቀጥላለች። የሎዛ ማርያም ድምቀት የተመሰከረለት ነው። እስከ ዛሬ ጥር እና ጎንደር ስንል ኖረናል። ወር ፈክታ አስራ አንድ ወር የምታቃስት ጎንደር በቃን ብለናል።
አስራ ሦስት ወር የምትሞሸር ከተማ ለመስራት ስንደክም በሀሳብም ሆነ በገንዘብ ላገዛችሁን ወዳጆቻችን ሁሉ በድጋሚ በእራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።